በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 97 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና አልፈዋል:-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 97 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና አልፈዋል:-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ ሐምሌ፣13/2018 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ የ2018 ዓ/ም የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የፈተና ውጤትበማስመልከት ለመገናኛ ብዙሀን በጽ/ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት በክልሉ በትምህርት ዘመኑ 1ሺ 538 ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የፈተና ማስፈተናቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አብራርተዋል። በክልሉ 42ሺ 966 ወንድ እንዲሁም 42ሺ 565 ሴት በድምሩ 85ሺ 531 ተማሪዎች ለፈተና መቅረባቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። በክልሉ ፈተና ከተሰጣቸው ተማሪዎች ውስጥ 41ሺ 951 ወንዶች እንዲሁም 41ሺ 391 ሴቶች በድምሩ 83ሺ 342 ወይም 97 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ስለማስመዝገባቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። በክልሉ የ2018 የትምህርት ዘመን ውጤት ከ2017 ዓ/ም ጋር ሲነጻጸር በ61 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ አንተነህ አብራርተዋል። በክልሉ ጠንካራ የፈተና አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም በክልል፣በዞን በወረዳ እና በከተማ አስተዳደር 151 ሱፐር ቫይዘሮች ማሰማራት ተችሏል ብለዋል። በክልሉ ዘንድሮ ካስፈተኑ 1ሺ 538 ትምህርት ቤቶች ውስጥ1017 ትምህርት ቤቶች ሁሉንም ተማሪዎች ማሳለፍ ስለመቻላቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን ምንም ተማሪ ያላሳለፈ ትምህርት ቤት የለም ያሉት አቶ አንተነህ በ2017 ዓ/ም 268 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ ተስኗቸው እንደነበር አስታውሰዋል።በዘንድሮው አመት ይህ አሀዝ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አቶ አንተነህ ጠቁመዋል። ዘንድሮ ለተመዘገበው ውጤት መሻሻል በርካታ መንስኤዎች እንዳሉት የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም፣የመምህራን አቅም ግንባታ፣የግብአት አቅርቦት፣ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ በመፈጠሩ፣የተማሪዎች የትምህርት ተነሳሽነት መጨመር፣የመማር ማስተማር ስራ መሻሻል፣የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ፣የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ፣እና ሌሎችም ጉዳዮችን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ለዘንድሮው የፈተና ውጤት መሻሻል ክቡር ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው( ዶ/ር)የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ ( ዶ/ር)ከክልል እስከ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ባለው መዋቅር የሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች ፣የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ፣የጸጥታ አካላት፣ተማሪዎችየላቀ ተሳትፎ በማድረጋቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል። ስል የዘገበው የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ነው።